"I was choose by the Nobel prize Committee" Betty G -Ethiopian singer

admin
0


ሀገሬና 'ሲንጃለዳ' (Sin jaaladha) የተሰኘ የኦሮምኛ ሙዚቃዎቿን የተጫወተችው ቤቲ ጂ መድረኩ ላይ ስትወዛወዝም ታይቷል።
ባቀረበቻቸው የሙዚቃ ሥራዎች በተለይ በማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋጋሪያ ሆና ነበር። አድናቆትም ተችሯታል።
ቤቲ ጂ በዕለቱ ሥራዋን እንድታቀርብ የኖቤል ኮሚቴ ከመረጣት በኋላ በማኔጀሯ (በስራ አስኪያጇ) በኩል መመረጧን እንደነገሯትና ይህም ሁኔታ ''ትንግርት'' እንደሆነባት ለቢቢሲ ተናግራለች።

"'እኔ ነኝ የመረጥኩሽ' ያሉትን የኮሚቴ አባል አግኝቻቸው ነበር" የምትለው ድምጻዊት ብሩክታዊት "ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አንጋፋ ድምጻውያን ሁሉ ለይተው እኔን እንዴት መረጡኝ?" ብላ መጠየቋን ትናገራለች።
ቤቲ ጂ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ድምጻውያን ሁሉ እርሷን በመምረጣቸው ደስተኛ መሆኗን በመግለጽ፤ ምክንያታቸውን ብትጠይቃቸውም " አንቺን በመምረጣችን ደስተኛ ነኝ" ከማለት ውጪ መስፈርታቸውንም ሆነ ምክንያታቸውን እንዳልገለጹላት ታስረዳለች።
"እኔም የፈጣሪ ሥራ ብዬ ነው የማምነው" የምትለው ድምጻዊት ብሩክታዊት በሰላም ኖቤል ሽልማቱ ላይ እንደምትዘፍን ያወቀችው የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ድምጻዊት ቤቲ ጂ፣ ለዚህ ሥራዋ ምን ያህል እንደተከፈላት ተጠይቃ ስትመልስ ብዙ አለመሆኑንና ዋናው የሄደችበት ምክንያት ልክ እንደሌሎች አንጋፋ የሙያ ባልደረቦቿ ኢትዮጵያን ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ ነው ብላለች።
ቤቲ ጂ "ለኔ የኖቤል ሽልማቱ ዝግጅት ፍራቻና ደስታ የተሞላበት ነበር" ስትል ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ገልጻለች። ምክንያቷን ስታስረዳም "ንጉሥና ንግሥት ፊት መዝፈን በየጊዜው አያጋጥምም" በማለት የኢትዮጵያውያንን አደራ ተሸክማ ስትሰራ 'አበላሽ ይሆን?' የሚል ስጋትና ጭንቀት እንደነበረባት አልሸሸገችም።

በርግጥ ዝግጅቱ የደስታ ስሜትም ነበረው የምትለው ቤቲ፤ አክላም "እኔም በራሴ የኮራሁበት ሥራ ነው ማለት እችላለሁ" ብላለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በዕለቱ ሥራዋን እንደምታቀርብ እንደማያውቁና ለመጀመሪያ ጊዜ ያይዋት መድረክ ላይ ሥራዋን ስታቀርብ እንደሆነ ትናገራለች።
ይህ የሆነው ለእርሳቸው የኖቤል ሽልማቱን ያዘጋጁት አካላት እንደ 'ሰርፕራይዝ' በማሰባቸው መሆኑን ገልጻለች።
በዕለቱ የነበረው ዝግጅቷን በተመለከተ ስትናገር በርካቶች መውደዳቸውን እንደነገሯት ገልጻ እርሷ ደግሞ ሀገሬ የተሰኘውን ሙዚቃ ቪዲዮ ስታየው እንባ እንደሚተናነቃት ገልጻለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከመድረክ ስራዋን ካቀረበች በኋላ እንዳገኘቻቸውና " በጣም ጥሩ ሥራ ነው ያቀረብሽው፤ በርቺ" ማለታቸውን ታስታውሳለች።
የሙዚቃ ሥራዎቿን እርሷ እና የኖቤል ኮሚቴው በጋራ መምረጣቸውን የምትናገረው ድምጻዊት ብሩክታዊት ጌታሁን፣ 'ሲንጃለዳ' (Sin jaaladha) የተመረጠበትን ምክንያት ስታስረዳ በወቅቱ ከልብሷ እስከ ሙዚቃዋ ኢትዮጵያን ለመወከል በማሰብ መሆኑን ተናግራለች።
ቤቲ ጂ የለበሰችው የባህል ልብስና የፀጉር አሰራሯ ትግራይን፣ ሀገሬ ሙዚቃ አማርኛ ተናጋሪውን፣ 'በሲንጃለዳ' (Sin jaaladha) ደግሞ ኦሮሚያን ለመወከል አስባ መስራቷን ገልጻለች።
እጇን የተጌጠችበት የምስራቁን የኢትዮጵያ ክፍልን ለመወከል በማሰብ ይሁነኝ ተብሎ የተሠራ ነው።
ለኮሚቴው አባላት በሙዚቃ ምርጫዎቿ ወቅት የሙዚቃዎቹን ትርጉም በመላክ ለማስረዳት መሞከሯን በመናገርም "በነበረን አጭር ዝግጅት ጊዜ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አይቶት የሚወደው ሥራ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ" ብላለች።
'ሀገሬ' የሚለውም ሙዚቃ ከምን ጊዜውም በላይ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ምድሪቷና ሕዝቦቿ በጋራ ሲሆኑ እንደሚቻል የሚገልጽና ለበዓሉም ሆነ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መልዕክት የያዘ መሆኑን ትናገራለች።
'ሲንጃለዳን' (Sin jaaladha') ላይ ለመደነስ ሁለት ሳምንት መለማመዷን የምትናገረው ቤቲ መጀመሪያ አካባቢ ያዞራት እንደነበር፣ በኋላ ላይ ግን ለዳንሱ የሚረዳትን ሙዚቃ ካስገባች በኋላ መቀየር እንደማትችል ስለተረዳች በልምምዷ ጠንክራ መግፋቷን ገልፃለች።



'እጅ መንሳት'
ቤቲ ጂና የሙዚቃ ባንዱ ሥራቸውን ከማቅረባቸው በፊትም ሆነ በኋላ የመድረኩን እንግዶችና ታዳሚያን እጅ ሲነሱ ታይቷል። በኖርዌይ እንዲህ ዓይነት መርሃ ግብሮች ላይ ንጉሳውያን ቤተሰቦች እንዲሁም የኖቤል ሽልማት ተቀባዮች ሲኖሩ እጅ መንሳት ባህል መኖሩን ገልጻ፤ ሥራቸውን ሲጀምሩም ሲጨርሱም እጅ መንሳታቸውን ለዚያ መሆኑን ትናገራለች።
"እኛ ኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ ባህል ስላለን ስንሰለጥን ብዙ አላስቸገርናቸውም።" ብላለች።
የሙዚቃ ሥራዋን ከማቅረቧ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከኖርዌጂያን ተቀባዮቿ ጋር ረዥም ልምምድ ማድረጓን በመጥቀስም፣ ከዚህ ቀደም ባለው ጊዜ ከኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጋር በሀገር ቤት ልምምድ ስታደርግ መቆየቷን ገልጻለች።
ቤቲ ልምምዶቹን ቀርጻ ለተቀባይዎቿ ትልክ ነበር። በአጠቃላይ የሁለት ሳምንት ልምምድም ፈጅቶባታል።
ሀገሬን ስትዘፍንም ኖርዌጂያን ተቀባዮች እየተቀበሏት መዝፈናቸው የተለየ ስሜት እንደፈጠረባትም አልሸሸገችም።
ኦሮምኛ ባትናገርም ቃላቶቹን ማጥናቷን የምትናገረው ድምጻዊት ብሩክታዊት፣ ከዚህ በፊት ወላይትኛ ስትዘፍንም ቃላቱን በማጥናት መሥራቷን ታስታውሳለች።
በወላይትኛ የዘፈነችውና በቅርቡ የሚለቀቅ ሙዚቃዋ ክሊፑ እየተሠራ ነው።
በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለመዝፈን ፍላጎት እንዳላት ገልጻ ከከፋ ብሔረሰብ ሙዚቀኞች ጋር የሠራችው ሙዚቃም በቅርቡ ይወጣል። የሙዚቃ ክሊፑም ተሰርቶ አልቋል።
የሙዚቃ ድግሶች ላይ በርካታ አድናቂዎች ባሉበት መጫወት እና በተጋባዥ እንግዶች ፊት መጫወት ያለውን ልዩነት ስታስረዳም "የሙዚቃ ድግስ ለመታደም የሚመጣው አድናቂ ስለሚጮህ፣ አብሮ ስለሚዘፍን መድረክ ላይ ለሚጫወተው ሙዚቀኛ ስሜቱ ይጋባል" ትላለች።
እንደ ኖቤል ያለ፤ የተጋበዙ እንግዶች ባሉበት መጫወት ግን ከታዳሚው የሚመጣው እርጋታና ዝም ብለው በጥሞና እያንዳንዱን ቃል እየሰሙ መሆናቸውን ማወቅ ደስ ቢልም የሚፈጥረው የፍርሃት ስሜት እንዳለ ትናገራለች።
 #BBC

Post a Comment

0Comments
Post a Comment (0)
featured/opinion